ንስሓ እንዴት ልግባ?

በመጋቤ ምሥጢር አባ ኅሩይ ኤርምያስ

“ንስሓ ግቡ” የሚለውን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዘወትር መልእክት ሰምተው አልያም በንስሓ ሕይወት የሚኖሩ መንፈሳውያንን አይተው በመንፈሳዊ ቅንዓት በመነሣሣት ወይም ደግሞ ያሳለፉት ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌለበት በረከት አልባ የሕይወት ጉዞ አድክሟቸው ዕረፍትና ተስፋ በማጣት የዛለች ነፍሳቸውን ከእግዚአብሔር በሚገኝ ይርቅታ ከሥቃይ ለማሳረፍ በመሻት ብዙ ሰዎች ንስሓ መግባትን እየፈለጉ ንስሓ እንዴት እንደሚገባ ባለማወቅ ይቸገራሉ። አንዳንዶችም ንስሓ መግባት የሠሩትን ኀጢአትን በካህን ፊት ለእግዚአብሔር መናዘዝን የሚያስቀድም ተግባረ ነፍስ በመሆኑ ራስን መክሰስና መግለጥ እያስጨነቃቸው ፈራ ተባ በማለት የመቃተታቸውን ቀን ያራዝማሉ ነፃነታቸውንም ያርቃሉ።

አንተስ ንስሓ ገብተህ የነፍስ ነፃነትህን እንዳታገኝ በእነዚህና እነዚህን በመሳሰሉ አደናቃፊ አሳቦች ተይዘህ ንስሓ ለመግባት ተቸግረሀልን? ይህ አጭር ትምህርታዊ ጽሑፍ ንስሓ ለመግባት ምን፣ መቼ፣ እንዴት ማድረግ አለብኝ? የሚል ጥያቄ ላላቸው ሰዎች መጠነኛ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስለሆነ በጥሙና አንብበው!

ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመፈጸሙ እና ሕግ በማፍረሱ በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ንስሓ ይገባል፤ መግባትም ይኖርበታል። ንስሓ መግባት ማለትም እንድፈጽመው የታዘዝሁትን ባለመፈጸሜ እንድጠብቀው የተሠራልኝንም ሕግ በማፍረሴ በእግዚአብሔር ፊት በደለኛ ሆኛለሁ፤ ባለመታመኔና አምላኬን የሚያሳዝን ተግባር ፈጽሜ በመገኘቴም አፍሬያለሁ፣ አዝኛለሁ፣ ተጸጽቻለሁ ብሎ ኀጢአትን በመናዘዝ ከእግዚአብሔር ይቅርታን መጠየቅ ማለት ነው።

ይህ ሃይማኖታዊ ተግባር ሲከናወን በሚታይ ሥርዓት የማይታይ ጸጋ (ሥርየተ ኀጢአት) ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያሰጥ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ከሰባቱ ምሥጢራት አንዱ አድርጋ ትቆጥረዋለች። ካለማመን ወደማመን የሚመጡም አምነው ተጠምቀው በሃይማኖት የሚኖሩም ሁለቱም ወገኖች የበደል ሸክማቸውን የሚያራግፉበት ከኀጢአት ወጥመድ ነፃ የሚወጡበት በመሆኑ ለሁሉ የሚሰበክ ለተቀበለውም ሁሉ ያለገደብ ተደጋግሞ የሚፈጸም ሥርዓት ነው።

በደለኛነትህን ታምናለህን? 

የንስሓ መጀመሪያ ጥፋተኛነትን ማመን ነው! ኀጢአት በደል የለብኝም ብሎ ማሰብ በራሱ ግዙፍ ጥፋት ነው! በነቢያትና በሐዋርያት አንደበት የተነገረ የመንፈስ ቅዱስን ቃልም መፃረር ነው፤ መንፈስ ቅዱስ በነቢያት አንደበት “ሁሉ ተካክሎ በደለ መልካምን የሚያደርጋት የለም” (መዝ ፲፫፥፫) ፤  “ጻድቅ የለም ጥበበኛም የለም?” (ሮሜ ፫፥፲) ብሎ ተናግሯልና። ኀጢአተኛ ነኝ ብሎ ማሰብና ማመን ግን እንዲጸጸቱ ያደርጋል፣ በደልኹት የሚሉትንም ወገን ይቅርታ ለመጠየቅና ለመካስ ያነሣሣል፤ ይቅር ለመባልም በእጅጉ ይረዳል። ለዚህም የጠፋው ልጅ እና የጥጦስ ታሪክ ደገኛ ምስክር ነው። የጠፋው ልጅ ይቅርታን ለመጠየቅና ለመቀበል ያበቃው በውድቀቱ ጊዜ አባቴን በድዬዋለሁ ብሎበደለኛነቱን ማመኑና አባቱንም “አባት ሆይ በሰማይም በፊትህም በደልኩ” በማለት ይቅርታ መጠየቁ ነው። (ሉቃ ፲፭፥፳፩) ቀማኛና ቋንጃ ቆራጭ ጥጦስም ከጌታ ጎን ተሰቅሎ ሳለ “ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” የሚል የይቅርታና የምሕረት ድምፅ መስማት ያስቻለው “አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ” ብሎ መማፀኑ ነው፤ ለመማፀንም ያነሣሣው ቅጣት የሚገባው በደለኛ መሆኑን አምኖ “እኛስ የሚገባንን በእውነት አገኘን እንደ ሥራችንም ተከፈለን” ብሎ በደለኛነቱን ማመኑ ነው። (ሉቃ ፳፫፥፵፩) 

ነሳሒ ሆይ፣ መጻሕፍት እንደሚነግሩን ከሰው ወገን አምላክን ከወለደች ከድንግል ማርያም በቀር ከኀጢአት ፈጽሞ ንጹሕ የሆነ የለምና በንጽሕና እንደ ቅድስት ድንግል አለመሆንህን በንስሓ ከታደሱ ከልዑል ቅዱሳንም የምትሻል አለመሆንህን ተረድተህ ሕጉን በማፍረስ አልያም ትእዛዙን ባለመፈጸም በመሥራት ወይም በመናገር ወይም ደግሞ በማሰብ የበደልህና የምትበድል መሆንህን እመን። አልበደልኩም አትበል፤ ይልቁንም ወደ ምሕረቱ ሰገነት እንዲያደርስህ የእግዚአብሔር  ቸርነቱ የሚያኖረኝ በደለኛ ነኝ በል። በዚህ ጊዜ መንፈሰ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት የተማረበትን ቅዱስ ጴጥሮስም ይቅር የተባለበትን የንስሓ ጎዳና ያመለክትሀል፣ ኀይል ጽንዕ ሆኖ ከምሕረት ደጃፎች ያደርስሀል።

በሁለተኛ ደረጃ እግዚአብሔር የሰዎችን መዳን የሚሻ ቸር አምላክ በመሆኑ ኀጢአተኞች ከክፉ ሥራቸው ተመልሰው ይድኑበት ዘንድ ንስሓን እንደሠራና ንስሓ በእውነት ሥርየተ ኀጢአትን የሚያስገኝ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቂያ የድኅነት ምክንያት መሆኑን ያለመጠራጠር እመን። አዳኝ በሆነ በክርስቶስ ስም ከመጠመቅህ ጋር ከፍርድ መዳን የሚቻልህ ንስሓ በመግባትህ ነውና “አሁንም ንስሓ ግቡ ተጠመቁም ኀጢአታችሁም ይደመሰስላችኋል” እንዲል። (ሐዋ፫፥፲፱)

በደለኛነቴን አምኛለሁ፤ ምን ላድርግ?

ነሳሒ ሆይ! ንስሓ መግባት የሚገባህ በደለኛ መሆንህንና ንስሓም ወደ ጽድቅ ሕይወት ለመመለስ የተሠራለህ መሆኑንካመንህ ዘንድ የንስሓ ሕይወት ጉዞህን ጀምረሀልና መመለስህን እንጂ ባዝነህ መቅረትህን መዳንህን እንጂ መጥፋትህን የማይፈልግ እግዚአብሔር ጉዞህን በምክርና በተግሣጽ ቀኖና በመስጠትና ለፍጻሜው በጸሎት የሚያግዝህ በምክር የሚያበረታህ መምህረ ንስሓ አዘጋጅቶልሀልና ፈጥነህ ወደ መምህረ ንስሓህ ገሥግሥ፤ ባገኘኻቸውም ጊዜ አባቴ በክፉ አሳቤና ሥራዬ ፈጣሪዬን በድያለሁ፤ አሁን ግን ተመልሻለሁ፤ የኀጢአቴን ኑዛዜ ይቀበሉኝ፣ እፈጽመው ዘንድ የሚገባኝንም ቀኖና ይስጡኝ፤ ስለበደሌ መደምሰስ ይጸልዩልኝ፣ ከኀጢአቴ ማሠሪያ ተፈትቼ ጌታዬ ክርስቶስ ከንፁሓን በጎቹ  ጋር ይቆጥረኝ ዘንድ ወደ ፈጣሪዬ ያቅርቡኝ ብለህ መመለስህን አብስራቸው። “በጎቼን ጠብቅ” (ዮሐ ፳፩፥፲፮) የሚለውን አምላካዊ አደራ በክህነታዊ መዐርጋቸው ከቅዱስ ጴጥሮስ በቅብብል የተረከቡ ባለአደራ ናቸውና በደስታ ይቀበሉሀል፤ ቁስለ ኀዘንህን በበጎ ምክራቸው ያክሙልሀል፤ ከክርስቶስ አንድነት የለየህን የኀጢአት ሸክም ገሥጸውና ናዝዘው ያራግፉልሀል። በሕሊናህ ውስጥ የሚመላለሰውን በደልህን ሁሉ ሳትሸሽግ ካህኑን ምስክር አድርገህ ለመንፈስቅዱስ ተናዘዝ፤ የነፍስ ቅጣቷ ማፈር መደንገጥ ነውና ማፈርህን አትጥላው፤ መደንገጥህን አትንቀፈው፤ ብትችልስ እንደ ዳዊት እንደ ጴጥሮስ በጸጸት እንባ ፊትህን አርስ፣ ነፍስህን አስጨንቃት።

ነሳሒ ሆይ! የበደልኹት እግዚአብሔርን ለምን ለካህን እናዘዛለሁ አትበል። “ሂድ ራስህን ለካህን አስመርምር” (ማቴ ፰፥፬) ብሎ ኀጢአትን በካህን ፊት መናዘዝን ያዘዘው ንስሓን የሠራና የሚቀበል እርሱ ፈጣሪ ነው። ካህን በአንተና በእግዚአብሔር መካከል ለምስክርነት ይቁም እንጂ የምትናዘዘው ለእግዚአብሔር ነውና፤ ይቅር የሚልህም እርሱ ነውና ቅዱስ ዮሐንስ “ኀጢአታችንን አምነን ብንናዘዝ ግን እርሱ ኀጢአታችንን ይቅር ለማለት የታመነና ጻድቅ ነው” እንዳለ። (፩ ዮሐ ፩፥፱)

ስለዚህ በደልህን ለመደበቅ ወይም ምክንያታዊ ለማድረግ አትሞክር፤ መንፈስ ቅዱስን መዋሸት እንዳይሆንብህ ይህን ከማድረግ ተጠበቅ። መንፈስ ቅዱስን ለመዋሸት መሞከርም እንደ ሐናንያና ሰጲራ ሞትን የሚያስፈርድ ታላቅ በደል መሆኑንም አትዘንጋ። (ሐዋ ፭፥፩-፲ ) ዳግመኛም “በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሠረ ይሁን በምድርም የፈታችሁት በሰማይም የተፈታ ይሁን” (ዮሐ ፳፥፳፫) ብሎ ጌታ ለመጀመሪያዎቹ የሐዲስ ኪዳን ካህናት (ሐዋርያት) ሥልጣነ ክህነትን የሰጣቸው ይቅር የሚል እርሱ ራሱ ሲሆን ይቅር መባላችን ግን በሾማቸው በካህናት በኩል እንዲሆን ስለፈቀደ መሆኑን  አምነህ ወደ ካህኑ ስትቀርብ በፍጹም እምነትና በጽኑ ተስፋ በመታመንና በአክብሮት ሊሆን ይገባል።

ቀኖናህን ፈጽም!

ነሳሒ ሆይ! ኀጢአት ያለቀኖና አይፋቅምና በደልህን በካህን ፊት ለእግዚአብሔር ከተናዘዝህ በኋላ ካህኑ ስለፈጸምኸው በደል ምሕረትን ስትሻ እግዚአብሔርን ደጅ ትጠና ዘንድ ቀኖና ይሠሩልሀል። ይህን ያህል ሱባኤ ጹም፣ ጸልይ፣ መጽውት፣ ስገድ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብብ፣ ወዘተርፈ ብለው ልትፈጽመው የምትችለውን መንፈሳዊ ተግባር ያዙሀል። ወደ ፈጣሪህ ከልብ መመለስህን፣ ለእርሡ መገዛትህን፣ መታዘዝህን በተግባር የምታረጋግጥበት ነውና አነሰ ብለህ ሳትጨምር በዛ ብለህ ሳትቀንስ የታዘዝኸውን በደስታና በታዛዥነት መንፈስ ፈጽም። እግዚአብሔርን ከመሥዋዕት ይልቅ ደስ የሚያሰኘው የሰው በጎ ተግባር መታዘዙ ነውና። (፩ ሳሙ ፲፭፥፳፪) 

ቀኖናህን በፈጸምህ ጊዜ ካህኑ ጸሎተ አስተሥርዮ አድርሰው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በተሰጠ መንፈሳዊ ሥልጣን “ከኀጢአት ማሠሪያ እግዚአብሔር ይፍታህ” ብለው መፈታትህን ያውጁልሀል፤ በዚህን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ፍጹም የሆነ ሥርየተ ኀጢአትን ይሰጥሀል። መስተዋት ታጥቦ እንዲጠራ ንስሓህን ምክንያት አድርጎ ከኀጢአትህ ያነፃሀል፣ ያጠራሀል፣ ያድስሀል። የጎሰቆለ ማንነትህን አስወግዶ የሚወደድ አዲስ ማንነትን ያጎናጽፍሀል፣ ለመንፈሳዊ ሥራ የተመረጥህ ማደሪያው ያደርግሀል። ይህ ሁሉ ታዲያ የሚፈጸምልህ ይሆንልኛል ይደረግልኛል ብሎ በማመን ነውና በእውነት ለምነኸው ችላ እንደማይልህ፣ በልብ ንፅሕና ተማፅነኸው ፊትን እንደማይመልስብህ ልመናህን ተቀብሎ ወደ ክብር እንደመለሰህ ያለመጠራጠር እመን መጽሐፍ “ንስሓ የበደለውን ሰው እንዳልበደለ አመንዝራውንም እንደ ድንግል ታደርገዋለች” ይላልና። ሃይ/አበ

አትታበይ፤ አመስግን እንጂ!

ነገር ግን ይቅር መባልህ ከእግዚአብሔር ቸርነት የተነሣ እንጂ በስግደትህና በጾም ብዛት እንዳልሆነ ለፈጸምኸውም ለእያንዳንዱ በደል ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት መቀጣት ሳያሻህ መታዘዝህን የምትገልጥበትን ጥቂት ቀኖና ብቻ መፈጸምህን ለአፍታም አትዘነጋ፤ እንደ ግብዝም ንስሓ በመግባቴ በመጾሜ በመስገዴ ከኀጢአቴ ነፃሁ አትበል።በእውነተኛ ንስሓቸው እንደተጠቀሙ የልዑል አምላክ አገልጋዮች በቸርነቱ አቀረበኝ፣ ሳይገባኝ አከበረኝ ብለህ ከባዘንክበት የሰበሰበህን ከጥፋት በንስሓ የመለሰኸንና ሸካራና ስለታሙን የኀጢአት ቀንበር ከጫንቃህ ላይ አንሥቶ ልዝቡን የልጅነት ቀንበር ያሲያዘህን ፈጣሪህን አመስግን ቸርነቱንም መስክር እንጂ።

በሥጋ ወደሙ ንስሓህን አትም!

ነሳሒ ሆይ! የንስሓ መደምደሚያው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነውና በደልህን አምነህና ተናዝዘህ ቀኖናህንም ፈጽመህ በካህን አብሳሪነት ከኀጢአት ማሠሪያ መፈታትህን የሰውን ድኅነት ከማይሻ ከዲያብሎስ አገዛዝም ነፃ መውጣትህን በሰማህ ጊዜ ርኩሱን የሚቀድሰውን ያደፈውን የሚያነፃውን የክርስቶስን ሥጋና ደም በንፅሕናና በትሕትና ሆነህ ተቀበል። በር ኖሮህ ካልዘጋኸው ቤትህ አይጠበቅም፣ ኀጢአትህን ተናዝዘህም ስታበቃ ሥጋ አምላክ ካልተቀበልኽበት መመለስህ የተፈጸመ አይሆንምና መቁረቡ እንኳ ይቆየኝ አትበል፤ ያለቁርባን ጥምቀት እንደሌለ ንስሓም ያለቁርባን አይሆንምና ሥጋ አምላክ እንድትቀበል ካህኑ ሲያሰናብትህ ለመቀበል አትዘግይ! ከበደል መንፃታችን የሚፈጸምልን በክርስቶስ ሥጋና ደም ነውና “የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአታችን ሁሉ ያነፃናል” እንዲል። (፩ ዮሐ ፩፥፯)

ቃል ኪዳንህን ጠብቅ፤ ዳግመኛ ብትስት ደግመህ ፈጥነህ ንስሓ ግባ!

ነሳሒ ሆይ! ንስሓ ከማይሹ ከመላእክት ወገን ያይደለህ ንስሓ ከተሠራላቸው የአዳም ወገኖች በመሆንህ ኀጢአትህን ተናዝዘህ ቀኖናህን ተቀብለህ መመለስህንም የክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል አትመህ በንስሓ ሕይወት ከሚኖሩ መንፈሳውያን ጋር ማኅበርተኛ ሆነሀልና በዚህ ፈጽሞ ደስ ይበልህ! ከእንግዲህ ደስታና የነፍስ ዕረፍት ካለበት ከዚህ የሕይወት መደብ መቼም ቢሆን መውጣትን አትሻ! ኀጢአትህን ሁሉ በተናዘዝህ ጊዜ ዳግመኛ የተጥጸጸትክባቸውን ኀጢአቶች ሠርተህ ፈጣሪህን ላለማሳዘን ቃል መግባትህን አትርሳ፤ ስለዚህም ሕጉን ባለማፍረስ ትእዛዛቱንም ለመፈጸም በመትጋት ቃል ኪዳንህን ጠብቅ! ከመበደል ለመከልከል በምትጋደለው መጠን መንፈሰ እግዚአብሔር አቸናፊ ትሆን ዘንድ ይረዳሀልና። ነገር ግን ሥጋ ለባሽ እንደመሆንህ መጠን ዳግመኛ ብትስት ደግመህ ፈጥነህ ንስሓ ግባ፤ ንስሓ አለ ብለህ በድፍረት ኀጢአትን አታዘውትር እንጂ ስተህ ተሸንግለህ ድቀት ቢያገኝህ ወድቀህ አትቅር ፈጥነህ ተነሥ፤ ንስሓ ግባ። ጠቢቡ ሰሎሞን “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ሰባት ጊዜም ይነሣል” እንዳለ። (ምሳ ፳፬፥፲፮) በንስሓ ሕይወት መኖር ማለት ተስፋ ሳይቆርጡ ቢወድቁም ለመነሣት መጋደል ነውና።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *