ታሪክ

ኢትዮጵያ የክርስትናን እምነት የተቀበለችው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ሐዋርያው ፊልጶስ ባጠመቀው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካኝነት ነበር። ክርስትና በሀገሪቱ ይስፋፋ ዘንድ ፈጻሚና አስፈጻሚ የሆነችው ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ328 ዓ.ም. ብሔራዊት ሆና ሲኖዶሷን መሠረተች። 

የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረት በዚህ መልክ በሀገሪቱ ይተከል ዘንድ አስተዋጽዖ ያደረገው አባ ፍሬምናጦስ የተባሉት በትውልድ ሶርያዊ የሆኑ ነገር ግን በአክሱም ቤተ መንግሥት ያደጉት ነበሩ። ይህም የሆነው ይህ አባት ወደ አሌክሳንደሪያ ሄዶ ከቅዱስ አትናቴዎስ የጵጵስና ማዕረግ ከተቀበሉ በኋላ ነበር። የክርስትና ብርሃን በሀገሪቱ ይበራ ዘንድ ያደረጉትን አስተዋጽዖ ለማስታዎስ ኢትዮጵያውያን ይህንን ታላቅ አባት አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (የሰላም አባት፣ የብርሃን መገለጫ) በማለት ይጠሯቸዋል። ከ150 ዓመታት በኋላ ዘጠኙ ቅዱሳን ተብለው የሚታወቁት አባቶች መነኮሳት ከመካከለኛው ምሥራቅና ከትንሿ እስያ ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። 

እነዚህ ቅዱሳን አባቶች የምንኵስናን ሕይወት ለሀገሪቱ ከማስተዋወቃቸውም በተጨማሪ በርካታ ሃይማኖታዊ መጻሕፍትን ከአረማይክ እና ከዕብራይስጥ ወደ ግዕዝ ቋንቋ ተርጉመዋል። የሠለስቱ ምዕትን የሌሎቹንም ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ትምህርተ ሃይማኖት። በ451 ዓ.ም. በአንጾኪያ ከተደረገው ጉባኤ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት በመባል ከሚታወቁት ከቅብጥ፣ ከሶርያ፣ ከአርመን፣ ከማላንካራ (ሕንድ) እና ከኤርትራ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ተመሳሳይ እምነትና ቀኖና ትከተላለች። ቤተ ክርስቲያኗ በተለያዩ ጊዜያት በተነሡ ሃይማኖታዊ ጥቃቶችና ወረራዎች ሰለባ ሆናለች። ለምሳሌ በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለአርባ ዓመታት በገዛችው በንግሥት ዮዲት በቤተ ክርስቲያኗ እና በምእመኗ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል። 
በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግራኝ መሐመድ ወረራ አማካኝነት የደረሰው ዕልቂት እጅግ የከፋ ነበር። እንዲሁም በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢየሱሳውያን በሚባሉት ሚሲዮናውያን፣ በመሪው በአልፎንሶ ሜንዴዝና በተከታዮቹ አማካኝነት ከፍተኛ ጥቃት ደርሶባታል። በኋላም በአምስቱ ዓመታት የፋሺስት ጣሊያን ወረራ ዘመን (1928-1933 ዓ.ም) ከሙሶሊኒ ጋር በተደረገው የነጻነት ትግል ጳጳሳትና መነኮሳት እንዲሁም ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ካህናት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከሁለት ሺሕ በላይ የሚቆጠሩ ጥንታውያት አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ወድመዋል። እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኗ ጥንታውያት የብራና መጻሕፍት ተዘርፈው ተወስደዋል።