መንፈሳዊ አገልግሎት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ አገልግሎቶች ይሰጣሉ። የመጀመሪያው በቤተ መቅደስ በካህናትና በዲያቆናት አማካኝነት የሚከናወነው የቅዳሴ ሥርዓት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በመዘምራንና በሊቃውንት የሚሰጠው የማሕሌት፣ የሰዓታት፣ የፍትሐት፣ ወዘተ. አገልግሎት ነው። በቤተ ክርስቲያኗ በሚሰጡ አገልግሎቶች ምእመናን ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርጋሉ። በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚሰጥበት ጊዜ በአጽዋማት እና በክብረ በዓላት ይለያያል። በጾም ጊዜያት ቅዳሴ የሚጀመረው ከቀኑ በ7 ሰዓት ነው። አንድ የቅዳሴ ሥርዓት ቢያንስ 2 ሰዓት ያህል ይፈጃል። ሆኖም ግን ሰዓቱ እንደሁኔታው ሊያጥርም፣ ሊረዝምም ይችላል። በትንሣኤ እና በልደት ክብረ በዓላት ጊዜያት ቅዳሴ ከሌሊቱ በ6 ሰዓት ይጀመራል። በዕለተ እሑድ ቅዳሴ የሚጀመረው ከጥዋቱ በ12 ሰዓት ሲሆን በአንዳንድ ገዳማትና አድባራት ግን ከሌሊቱ በ11 ሰዓት ሊጀመር ይችላል። ቤተ ክርስቲያኗ በመጻሕፍት ቀኖናዋ መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስ ቁጥር 81 (ሰማንያ አሐዱ) ሲሆን 14 የቅዳሴ መጻሕፍት አሏት። መንፈሳዊ አገልግሎቱ የሚሰጠው ጥንታዊ የኢትዮጵያ ልሳን በኾነው በግዕዝ ቋንቋ ነው። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ሥርዓተ ቅዳሴው በከፊል በአማርኛ ቋንቋም ይከናወናል። ከቤተ መቅደስ ውጭ ያለው የሰዓታት እና የማሕሌት አከባበርና አገልግሎት እንደ ወቅቱ ይለያያል። በጾም ጊዜያት በዕለተ ሰንበት ለእሑድ አጥቢያ ከሌሊቱ 6 ሰዓት ጀምሮ ቅዳሴ እስከሚጀመር እስከ ጥዋቱ 1 ሰዓት ድረስ ሰዓታት እና እንደ ዕለቱ ማሕሌት ይቆማል። በተጨማሪም ሥርዓተ ቅዳሴው ማሳረጊያ ላይ ዕጣነ ሞገር የተሰኘው የቅኔ ዝማሬ ይኖራል።