አስተዳደር

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛው አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ሲኾን እሱም በቤተ ክርስቲያኗ ጠቅላላ መንፈሳዊ አአስተዳደር ላይ ሥልጣን ያለው ነው። የሚመራውም በቅዱስ ፓትርያርኩ ኾኖ መንፈሳዊ ጉባኤውን በዓመት ሁለት ጊዜ ያደርጋል። በየአካባቢው ያለውን የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ በበላይነት የሚመራ “ሀገረ ስብከት” የተሰኘ አስተዳደራዊ መዋቅር ሲኖር ሊቀ ጳጳሱ የሀገረ ስብከቱን የአስተዳደር ጉባኤ በሊቀ መንበርነት ይመራሉ። በዓመት አንድ ጊዜ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ይካሔዳል። ቅዱስ ፓርትያርኩም ጉባኤውን በሊቀመንበርነት ይመራሉ። በሀገረ ስብከት ሥር የየወረዳውን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የሚመሩት የወረዳ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤቶች ያሉ ሲኾን በእያንዳንዱ አጥቢያ ደግሞ የሰበካ ጉባኤያት አሉ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት አገልጋዮች ያሉ ሲኾን የመጀመሪያዎቹ በቤተ መቅደስ መደበኛ የቅዳሴ አገልግሎት የሚሰጡ ካህናትና ዲያቆናት ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ በማሕሌትና አገልግሎት በሰዓታት አገልግሎት ተሰማርተው ታቅፈው የሚያገለግሉበት የሰንበት ትምህርት ቤት መዋቅር አለ። ይህ ተቋም ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ማኅበረ ገዳማትም እንደዚሁ የየራሳቸው የአስተዳደር መዋቅሮች አሏቸው።