“አጽንዑ ቀዊመ በሃይማኖትክሙ – በሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ ኑሩ!“ ፩ ጴጥ ፭፥፱

መጋቤ ምሥጢር ዶ/ር ኅሩይ ኤርምያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ምሕረትና ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ፥ ዓለማትን ፈጥሮ የሚገዛ ፥ ቀዳማዊና ደኃራዊ በአንድነቱ ምንታዌ በሦስትነቱ ርባዔ ሳይኖርበት እንደ ባለጸጋ በሀብት እንደ ነገሥታት በጉልበት እንደ ጣዖት በሐሰት ያይደለ ለጽንዐ አምልኮቱ በሚገባ እውነተኛ ምስጋና እርሱን ለማመስገን በሚተጉ በሰማያውያን መላእክት ለአምልኮቱ በሚቀኑም ምድራውያን ቅዱሳን አንደበት ሲቀደስ ሲወደስ የሚኖር ቅዱስ፣ ቡሩክና ሕያው አምላክ እግዚአብሔር እንኳን በሰላምና በጤና ጠብቆ ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ አሸጋገራችሁ፤ አሸጋገረን። 

የተወደዳችሁ ክርስቶስ ኢየሱስ በደሙ ያከበራችሁ ለመንግሥቱም ያጫችሁ ውሉደ እግዚአብሔር ካህናት ምእመናን! ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር የሞት መልእክተኛ የጥፋት ምንደኛ ከሆነ የዓለም ፈቃድ ራሳችንን ለይተን የማይጠፋ ሰማያዊ ጸጋቸውን በሚጠፋ ሥጋዊ ምቾታቸው፤ በሰማያት የሚያነግሥ መንፈሳዊ ክብራቸውን ዕመቀ ዕመቃት በሚያወርድ ምድራዊ ተድላቸው ከለወጡ በማወቅም ባለማወቅም ለጥፋት ተላልፈው ከተሰጡ ዓለመኞች ጋር አብረን እንዳንባዘን አብረን እንዳንጠፋ በክብር በባለሟልነት ወደእርሱ የምንቀርብበትን የቅዱስ መንፈሱም ማደሪያዎች ሆነን የምንኖርበትን ሃይማኖት ሰጥቶናል። አሚንሰ ትሬስዮ ለዘኢሀለወ ከመ ዘሀለወ ሃይ/አበ እንዲል ሃይማኖት በሥጋዊ ዐይን የማይታየውን ሰማያዊ አምላክ በዐይነ ልቡና የሚያዩበት፤ በምድራውያን እጅ የማይናኘውንም ሰማያዊ መንግሥት የሚቃኙበት ረቂቅ መነጽር ነው። በሃይማኖት ካልሆነ በቀር ሰው በዙርያው ካለውና ዘወትር ከሚያየው ዓመጽና ግፍ ከሞላበት ሞትና መከራ ከወደቀበት ግዙፍ ዓለም በቀር ከሞት በኋላ የሚወረስ ፍጻሜ ለሌለውም ጊዜ በመንፈሳዊ ደስታና በምስጋና የሚኖሩበት መንፈሳዊ ዓለም እንዳለ አሻግሮ ማየት ወይም እንዳለ ቢሰማም እንኳ በርግጥ አለ ብሎ አምኖ ለመቀበል አይችልም። ይህ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ የሰውን ልጅ ከፈጣሪው ሲለይና ዓለምን በመቅሠፍት ሲያስመታ የኖረ የበደልና የውድቀት መጀመሪያ ነው። በአንጻሩ በሃይማኖት ጋሻነት ጥንተ ጠላት ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ተዋግተው ድል ነሥተው ከፈጣሪያቸው ጋር ሊኖሩ የታደሉ ስማቸውም በሕይወት መዝገብ የተጻፈላቸው ቅዱሳን ጽኑዐን ብዙዎች ናቸው። 

በሃይማኖት እንደ ሄኖክ በዐለም ላይ ከተቃጣ መከራ በረድኤተ እግዚአብሔር ማምለጥ ይቻላል፤ እንደ አብርሃምም በማያውቁት ሀገር ባለርስት መሆን ይቻላል፤ እንደ ሣራ ከደከሙና ተስፋ ከቆረጡ በኋላ በበረከትና በደስታ መሞላት፤ እንደ ዳዊትም በጠላት ላይ አቸናፊ መሆን ይቻላል። ያለ ሃይማኖት ግን እግዚአብሔርን ማወቅም ማገልገልም ከቶ አይቻልም። ዕብ ፲፩፥፮ 

ዛሬ በዐለማችን ሀልዎተ እግዚአብሔርን የዘነጉ ብዙዎች ናቸው፤ ሃይማኖተኛ መሆንን የናቁና የሚጸየፉ ብዙዎች ናቸው፤ ከመቼውም ጊዜ የከፋ ኃጢአትና ወንጀል በዓለማችን ላይ ሲፈጸም ቢታይና ቢሰማ እንደነዚህ ዐይነቶቹ እግዚአብሔርን ማወቅም ማመንም ከማይፈልጉ ተስፋ የቆረጡ ወገኖች መካከል የሚመጣና የሚንሸራሸር ከንቱና ሰይጣናዊ አሳብ በሚመነጭ የኃጢአተኛነት ጉምጅት እንጂ በሃይማኖት ከሚኖሩ ሰዎች የሚታሰቡ ሊሆኑ አይችሉም። ዓለምን ጎርፍ ቢያጥለቀልቃት ሰደድ እሳት ቢለበልባት ይህን የመሰለው ሁሉ አስደንጋጭ መከራ ቢፈራረቅባት ይህ ሁሉ ማመንም መታመንም ካልቻለው የሰው ልጅ ሥራ አንጻር በዛ የሚባል መቅሠፍት አይሆንም። በሃይማኖት ቅጽር ውስጥ ተከበው ያሉትማ ፈጣሪያቸው ስለቃልኪዳኑ እየጠበቃቸው እንጂ ያልገፏት ዓለም እየገፋቻቸው፣ ያልበደሉት የሰው ወገን አስጨንቆ እየጎሰማቸው ለዐለም ባይተዋሮች ሆነው ይኖራሉ እንጂ ለዚህ ዓለም ርኵሰትና ጥፋት ተባባሪዎች አይደሉም። ለበጎ ምእመናን ዓለማቸው አምላካቸው፤ ክብራቸው ወንጌል፤ ተድላቸው የጸጋ ልጅነታቸው፤ አሳባቸው ንስሓ ፤ ዜማቸው ጸሎት ትርፋቸው በረከት ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር ብቻ የሚገኝና አንዴ ካገኙትም መልሰው የማያጡት አጋንንት በተንኮላቸው የማይናጠቁት የማይጠፋ ጸጋና ሀብት በመሆኑ በዓለም ካለው ሁሉ ሊወዳደረው የሚችል አንዳችም ነገር የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ሉቃ ፲፥፵፪ 

እንግዲህ አምላካችንን ዕለት ዕለት የምናመሰግንበት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩንም ከምንም በላይ እርሱን የምናውቅበትን ፤ በጸጋ ከአብራከ መንፈስቅዱስ ተወልደን አባ አባት ሆይ ብለን እርሱን የምንጠራበትን የልጅነት ጸጋ የተጎናጸፍንበትን፣ ልጆቼ ተብለን በአምላካችን አንደበት የምንጠራበትን፣ የመላእክትን አንድነት በቅዳሴ በውዳሴ የቅዱሳንንም ኅብረት በምግባር በትሩፋት የምንሳተፍበትን ከሀብት ሁሉ የላቀ ረቂቁን ሀብት ሃይማኖትን ስለሰጠን አልቀን እናመሰግነዋለን ስሙንም ስናወድስ እንኖራለን። 

ለመንፈሳዊ ሥራ መነሣሣታችን፣ ስለ በጎ ሥራ መከራን መታገሣችን፣ ስለ እውነት መድከማችን በሃይማኖት ስለሃይማኖት እንጂ በሌላ በምንም ምክንያት አይሆንም። የሃይማኖት ፍቅር በውስጣችን ባይነግሥ ኖሮ ሃይማኖት እንደ ተረት በተቆጠረበት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እኛ ቤተ ክርስቲያን ስንሠራ መቅደስ ስናንጽ፣ መጻሕፍት ስንጽፍና ስንተረጉም፣ ስንቀድስ ስናወድስ አንገኝም ነበረ፤ ምናልባት እንደሌሎቹ ሠለጠን ባዮች ሁሉ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሸጠን ዋጋውን ስንካፈል እንገኝ ነበር ይሆናል። አምላካችን በተለይ ለእኛ ለምንፈራው የሚያደርግልን ቸርነቱ ብዙ ስለሆነ ከድኅነት ሁሉ የሚከፋው የሃይማኖት ድኅነት የአእምሮ ድኅነት እንዳያገኘን ጥበቃው አልተለየንም። ከዓመት እስከ ዓመት መሥዋዕት ከሚሠዋባት ቅድስት ሀገራችን በተለያየ ምክንያት ወጥተን በማናውቀው ሀገር ብንኖር እንኳ ቀድሰን የምንቀደስበት፣ ቃሉን ሰምተን የምንፈወስበት፣ አመስግነን በረከት የምናገኝበት ቤተ ክርስቲያን እንዲኖረን ከአምልኮቱ ከምስጋናው እንዳንለይ ረድቶናል። በባዕድ ሀገር አገኘን ብለን ልንደሰትበት ከሚገባን መልካም ነገር አንዱና ዋንኛው ሊሆን የሚገባው እንግዲህ ይህ ነው። ሌላውማ ድንገት እንደተገኘ ድንገት የሚጠፋ ፤ ድንገት እንደሞላ ድንገት የሚጎድል መሆኑን እያየን እየተመለከትን ነው። 

ሃይማኖት ለሚታመኑ ሰዎች ግዳጅ የሚያስፈጽም የሹትን የሚያስገኝ እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ሃይማኖትሰ ጥይቅት ይእቲ ለዘይሴፈዋ = ሃይማኖትስ ተስፋ ለሚያደርጋት የታመነች ናት ዕብ ፲፩፥፩ ሲል መስክሯል። በሃይማኖት ታመው የተፈወሱ፣ ወድቀው የተነሡ ብዙ ደጋግ ሰዎችንም በመጽሐፍ ቅዱስም በድርሳናትና በገድላትም ታሪካቸው ተጽፎልን ዐወቀናል። የሃይማኖት ሰዎች ታሪካቸው ገድላቸው መጻፉ መተርጎሙም ያስፈለገው አንዱና ዋንኛው ጥቅሙ ሃይማኖት ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ድልድይ፣ በጎ ሥራ ለማሠራት የሚያነሣሣ፣ የሚያደፋፍርና አስጀምሮ የሚያስፈጽም ረቂቅ ኀይል፤ በጥቂት መከራና ድካም የማይሰፈር ብዙ የብዙ ብዙ ምድራዊና ሰማያዊ ጸጋ የሚያሰጥ መሆኑን በጎላ በተረዳ ነገር ተገንዝበን ፍለጋቸውን እንድንከተል ነው። ወገኖቼ ሃይማኖታችን ለእኛ ሀብታችን ነው! ሃይማኖታችን ጌጣችንና ብልጥግናችን ነው! ሃይማኖታችን ኀይላችንና ጥበባችን ነው! ጨዋነታችን፣ ደግነታችን፣ መተዛዘናችን፣ ለበጎ ሥራ መሽቀዳደማችን ይህ ሁሉ ሃይማኖታቸውን በጠዋቱ የጣሉ ይሉኝታቢሶች የሌላቸው ሃይማኖታችን ያስተማረንና ያወረሰን የማናፍርበት ይልቁንም የምንኮራበት የማንነታችን መገለጫ ነው። ስለዚህም ወገኖቼ የፍቅርና የሰላም አምላክ ለሆነ አምላካችን አገልጋዮች አድርጎ ያቆመንን፤ ለፍቅር እናት ለድንግል ማርያም የቤቷ አገልጋዮች አድርጎ ያሰለፈንን ሃይማኖታችንን በማንኛውም ሥጋዊ ምድራዊ ፈተና ሳንሸነፍ አጥብቀን ልንይዝ ይገባል፤ ለበጎ ሥራችን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ሁሉ መሠረቱ እርሱ ነውና። ሃይማኖታችንን መዋል ብቻ አይደለም ልናድርበት ማደርም ብቻ አይደለም ልንኖርበት ይገባል፤ ከሃይማኖት የተሻለ ሊኖሩበት የሚመች ሊኖሩበት የሚያስጎመጅ የለምና። ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ነፍሳቸው አጽንታ የምትሻውን መንፈሳዊ ተምኔት በገለጹበት አንቀጽ “አንሰ እፈቅድ ክርስቲያነ እሰመይ ወክርስቲያነ አሀሉ ክርስቲያነ አዐል ወክርስቲያነ እቢት በኵሉ መዋዕለ ሕይወትየ በከመ ትምህርተ አበውየ ሐዋርያት ወክርስቲያነ እኑም ውስተ ከርሠ መቃብር ከመ አበውየ ሐዋርያት ወክርስቲያነ እንቃህ በተንሥኦትየ ምስለ አበውየ ሐዋርያት == እኔ ክርስቲያን እባል ዘንድ ክርስቲያንም ሆኜ እኖር ዘንድ አሻለሁ፤ በዘመኔም ሁሉ እንደ አባቶቼ ሐዋርያት ትምህርት ክርስቲያን ሆኜ እውል ክርስቲያንም ሆኜ አድር ዘንድ እሻለሁ፤ እንደ አባቶቼ እንደ ሐዋርያት ክርስቲያን ሆኜ በመቃብር ውስጥ አንቀላፋ በምነሣም ጊዜ ከአባቶቼ ከሐዋርያት ጋር ክርስቲያን ሆኜ እነሣ ዘንድ እሻለሁ” (መጽ/ምሥ ፲፥፪) ማለታቸው ይህን እውነት ከመረዳትና አጥብቆ ከመሻት የተነሣ ነው። 

ወገኖቼ! በዓለም ውስጥ ሊገኝ የሚችለው ትልቁ ዋጋ ወርቅ ወይም አልማዝ ነው፤ በሃይማኖት ግን የሚገኘው ሕይወት ነው .. ዘለዓለማዊ ሕይወት። በሃይማኖታችን ላይ የሚገዳደሩትን የጥፋት መልእከተኞች ስናይ በትዕግሥታቸው የእግዚአብሔርን መንግሥት የወረሱ የቀደሙ አባቶቻችንን እናስባቸው! በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ተደራጅተው የተነሡትን አሳዳጆች ስንመለከት በሊብያ በረሀ በሃይማኖታችን አንደራደርም ብለው መራራ ሞትን የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት እናስታውሳቸው! በሃይማኖታችን ምክንያት በሥራችን፣ በትምህርታችን በኖሮአችንም ሁሉ ባላጋራ ሲበረታብን ስለሃይማኖታቸው ስለቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸውም ብለው ሳይበድሉ የተበደሉትን ማንንም ሳያስቀይሙ በጥይት ተደብድበው በእሳት ተቃጥለው በገጀራ ተተርትረው የጊዮርጊስን ሞት የሞቱትን እየሞቱም ያሉትን የዘመናችንን ድንቅ የተዋሕዶ ከዋክብት እናስባቸው! መከራው ቢበዛም ፈተናውም ቢበረታም በክርስቶስ ደም የተመሠረተች ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ክፉ ጊዜ ማለፏ፤ ለልጅ ልጅም መድረሷ አይቀርም። መከራ ሊያጸናን እንጂ ሊያንበረክከን ኀዘኑም ሊያበረታችን እንጂ አንገት ሊያስደፋን አይገባም። እኛ የድል አድራጊው የክርስቶስ ልጆች ነን! በእምነታችን ሽንፈት የለብንም! ተንኮልን የተጫሙ ራስ ወዳድነትን የተጎናጸፉ የጽድቅና የሰላም ጠላቶች የቱንም ዐይነት መከራ ቢደግሡልን በሃይማኖት ምክንያት የሚያገኘንን መከራ በታገሥን መጠል የሚጠብቀን መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ ወንሕነሰ ንትዔገሥ ወንጸንዕ ከመ ንንሣእ አክሊለ ዘኢየኀልፍእኛ ግን የማይልፈውን አክሊል ለማግኘት እንታገሣለን እንጸናለንም“” (፩ ቆሮ ፱፥፳፮) ብሎ እንዳስተማረን ዘለዓለማዊ ክብር ዘለዓለማዊ ደስታ መሆኑን እያሰብን በሃይማኖት ስለሃይማኖት ጸንተን እንኖራለን እንጂ ክርስቶስን ከማመንና ከማመስገን ለአፍታም ወደ ኋላ አናፈገፍግም።   

የሰላም አምላክ በረድኤቱ ይጠብቀን! ሀገራችን ኢትዮጵያን ሕዝበ ክርስቲያኑንም ሁሉ በቸርነቱ ይጠብቅልን!  ዘመነ ዮሐንስን የቤተ ክርስቲያናችን ክብሯ፣ ነፃነቷና ሰላሟ የሚመለስበት፤ መከራን ታግሠው ለሚኖሩ ሎቿም የእፎይታና የበረከት ዘመን ያድርግልን!       

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!