“እስመ ኢየሱስ ክርስቶስ መጽአ ውስተ ዓለም ከመ ያድኅኖሙ ለኃጥአን … ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ሊያድን ወደ ዓለም መጥቷልና“ ፩ ጢሞ ፩፥፲፭

መጋቤ ምሥጢር ዶ/ር ኅሩይ ኤርምያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

         ቸርነትና ይቅርታ የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ፥ ዓለማትን የፈጠረ ፥ ቀዳማዊና ደኃራዊ በአንድነቱ ምንታዌ በሦስትነቱ ርባዔ ሳይኖርበት እንደባለጸጋ በሀብት እንደ ነገሥታት በጉልበት እንደ ጣዖት በሐሰት ያይደለ ለንጽሐ ባሕርዩ ለጽንዐ አምልኮቱ በሚገባ እውነተኛ ምስጋና እርሱን ለማመስገን በሚተጉ በመላእክት ለአምልኮቱ በሚቀኑም ቅዱሳን ሰዎች አንደበት ሲቀደስ ሲወደስ የሚኖር ቅዱስ ቡሩክ ሕያው አምላክ እግዚአብሔር እንኳን በሰላምና በጤና ጠብቆ ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ!

        በክርስቶስ ኢየሱስ ስም አምነንና ተጠምቀን ከስሞችም በላይ በሆነ ስሙ ክርስቲያን ተብለን ተላውያነ ክርስቶስ ሆነን የምንኖር ምእመናን በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ሳናቋርጥ በየዓመቱ በምስጋናና በፍጹም ደስታ ከምናከብራቸው ዐበይት በዓላት አንዱ በዓለ ልደት ነው። ይህንን በዓል የጌታ ከድንግል መወለድ በታወቀባት ሌሊት የሰማይ መላእክትና ምድራውያን እረኞች ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእበሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ፍቅሩ ለሰው ልጆች ሆነ ብሎ በመዘመር ፤ ግሑሳንም ከእንስሳት ምልክቱን ተረድተው ዮም ተወልደ ለነ ከሣቴ ብርሃን፥ ዮም ተወልደ ለነ መድኃኔዓለም ብሎ በማወደስ ፥ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንም ትንቢት የተነገረለት ሱባዔ የተቆጠረለት መድኅን ተወለደልን ብሎ በማመስገን አክብረውታል። ሉቃ ፪፥፲፬ 

        ይህ ምስጋና ይህ ሥርዓት ሳይቋረጥ ዛሬም ድረስ በዓለ ልደት ባማረ ምስጋና በተወደደ ውዳሴ ይከበራል። እንደ መላእክቱና እንደ እረኞች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበን “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር“ እያልን በሐሤት እንዘምራለን ፤ ለዓለሙም ሁሉ “ዮም ተወልደ መድኃኔዓለም ፥ ዮም ተወልደ ቤዛ ኲሉ ዓለም“ ብለን እንመሰክራልን ። ሰማይ ዙፋኑ ምድርም በመላዋ የእግሩ መረገጫ የሆነችለት ሰማያዊ ጌታ በከብቶች በረት ውስጥ በግርግም ተኝቶ መገኘቱ ፥ አካሉ እሳት ልብሱ እሳት ተብሎ የሚመሰገን ጌታ ብርድ በጸናበት ወራት ተወልዶ እንስሳት እስትንፋሳቸውን ገብረው ሊያሞቁት መትጋታቸው አምላካችን ለሰው ልጆች ያለውን በጎ ፈቃድ ያየንበት ቸርነቱ ስለሆነ ይህን የተደረገልንን ውለታውን መቼም ቢሆን እንድንዘነጋው አያደርገንም ቸል እንድንልውም አይፈቅድልንም ። የሆነው ሁሉ ለርሱ ክብር ለርሱ ጌትነት ያይደለ ለሰው ልጆች ክብርና ብልጽግና በመሆኑ ምስጋናውን አልሰቸነውም ውዳሴውን አልጠገብነውም ፤ የመወለዱ ነገር ዛሬም ለጆሮዎቻችን ሕይወትነት ያለው አዲስ ዜና ነው፤ አምላክ ሥጋችንን ተዋህዶ ሰው ሲሆን ከወገኖቻችን መካከል የተገኘች በልቡናዋም በአንደበቷም ስህተት ግድፈት በሥጋዋም ርኲሰት ያልተገኘባት ድንግል እናታችን የአምላክ እናት የመሆኗ ምሥጢር ዛሬም ለእኛ ድንቅ የምስራች ነው። 

         ተወድዶ ወዳጅ ተፈቅሮ ፍቁር ታምኖ ታማኝ ሆኖ መገኘት ካልቻለ ንጽህናን እንደ ካባ ደርቦ እንዲኖር የተፈጠረ ባሕርዩን በረብ የለሽ ስስቱና ጉምጅቱ ካሳደፈ የሰው ልጅ መወለድ ምን ያጓጓ ነበር? ማኅበርተኞቹ መላእክት ከተለዩት ባላጋራዎቹ አጋንንት ካዋረዱት የሰው ልጅ ጋር መዛመድ ወገን መሆን ምን ደስ ያሰኝ ይሆን? ፍጡር ይህ አያደርገውም ፡ ለመውደዱ ወረት ለፍቅሩ እብለት የሌለበት ጌታ ግን ሥጋና ነፍስን ተዋህዶ ዘመድ ሆነለት ፤ በዘር ከተወለደች ድንግል ልጁም ያለዘር ተወልዶ ወገን አደረገው። ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ አስተርአየ ዘኢያስተርኢየማይታይ እርሱ ታየ የማይገለጥ እርሱ ተገለጠ ብሎ እንዳመሰገነ መከራ መስቀልን ወደ ኋላ አቆይቶ ስደተኛውን ቤተኛ ባሪያ መባል ያልተገባውን ወራሽ ልጅ ለማድረግ በሥጋ ተገለጠ። መወለዱ፣ ሰው መሆኑ፣ ሥጋን መዋሀዱ፣ በበረት መተኛቱ፣ ከእንስሳት እስትንፋስን ከአሕዛብ ነገሥታት እጅ መነሻን መቀበሉ ቅዱስ ጳውሎስ እስመ ኢየሱስ ክርስቶስ መጽአ ውስተ ዓለም ከመ ያድኅኖሙ ለኃጥአን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ሊያድን ወደ ዓለም መጥቷልና ፩ጢሞ ፩፥፲፭ እንዳለ በኃጢአት ያደፈውን የሰው ባሕርይ አድሶ አጽንቶ ሰውን ሁሉ ሕዝበ እግዚአብሔር ለማድረግ ነውና የቸርነቱ ብዛት የፍቅሩ ጽናት ሁሌም እንድናመሰግነው ዘወትር እንድናወድሰው ግድ ይለናል። 

        ለምእመናን ብቻ ያይደለ ለሕዝብና ለአሕዛብ ሁሉ ሞትን የሚያስፈርድ ወደ ገሃነም መውረድንም ከሚያስከትል  ፍዳ መርገም ሊያድነን የሚችለው የታመነው መድኃኒት ጌታ በርግጥ የሰው ልጆን ሁሉ ሊያድን ሰው ሆኗል ፤ ከራቅንበት ከባዘንበት ሊሰበስበን በክብር በባለሟልነትም ወደ ራሱ ሊያቀርበን የሚችለው ብቸኛ ጌታ በርግጥ ሰው ሆኖ ወገን አድርጎናል ፤ ክብር ያልነበረው ሥጋም በልዩ ጥበቡ ባደረገው ተዋህዶ ክቡር አምላክ የተባለበት ድንግልም ወላዲተ አምላክ የተባለችበት ድንቅ ምሥጢር ተፈጽሟል ኑ ይህን ድንቅ እዩ የመላእክትና የሰዎች አንድነት የተደረገባት የቤተልሔም ዋሻ ምሳሌ ወደ ሆነችላት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ተሰብሰቡ እንደጠሉኝ ልጥላቸው ሳይል በፍጹም ፍቅር ለወደደን እንደ ከዱኝ ልካዳቸው ሳይል በክብር በባለሟልነት ወደ ክብሩ ላቀረበን ጌታም ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ብላችሁ ምስጋናን አቅርቡ ፤ ሰው የሆነ እርሱ ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ ተብሎ በኢሳይያስ (ኢሳ ፱፥፮) የተነገረለት አምላክ ነው ፤ ሰው የሆነ እርሱ ነቢዩ ዳዊት እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድርእግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው በምድር መካከልም መድኃኒትን አደረገ መዝ ፸፫፥፲፪ ብሎ የዘመረለት የምድር መካከል በምትባል በጎልጎታ በመስቀል ተሰቅሎ በሞቱ ዓለምን ለማዳን የወደደ ሰማያዊ ንጉሥ እንደሆነ አውቃችሁ ከቊስለ ኃጢአት እንዲፈውሳችሁ ከውቅያኖስ ውኃ ከበዛ ጸጋውም እንዲያሳትፋችሁ እንደ ሰብአ ሰገል ወርቃችሁን ብቻ ሳይሆን ራሳችሁን ገብሩለት ሥጋችሁንና ነፍሳችሁን አስገዙለት ብለን እንመክራለን።

               “አብን የሚመስለው እርሱ ነፍሳችንን ከኃጢአት ፍዳ ያድን ዘንድ ከድንግል ተወለደ“ 

                                                  ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት ሃይ.አበ ፷፩፥፳፱ 

                                        በዓሉ የሰላምና የፍቅር የበረከት በዓል ይሁንልን!              

                                                           ወስብሐት ለእግዚአብሔር