አነ ውእቱ ገብርኤል ዘእቀውም ቅድመ እግዚአብሔር!

በመምህር ኅሩይ ኤርምያስ

        ገብርኤል የሚለው ስም የሁለት ቃላት ጥምረት ነው ገብር አገልጋይ ፣ ባለሟል ማለት ሲሆን ኤል ደግሞ ስመ አምላክ ነው ስለዚህም ገብርኤል ማለት የእግዚአብሔር ባለሟል ወይም አገልጋይ ማለት ነው። ልደተ ዮሐንስን ሊያበስር ወደ ዘካርያስ ተልኮ ሳለ ዘካርያስ ልጅ የማግኘት ተስፋው መንምኖበት ስለነበር የምስራቹን ቃል ለመቀበል በዘገየ ጊዜ የላኪውን ማንነት ቢያውቅ ኖሮ ተላኪው በሚደነቅ ግርማ ቢታየውም ምትሐት ባልመሰለው ቃሉንም ፈጥኖ በተቀበለው ነበርና “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝብሎታል (ሉቃ ፩፥፲፱) ይህንንም ማለቱ ቅሉ ለተልዕኮ ለአምልኮ ለምስጋና ለምልጃ ዘወትር በአምላክ ፊት የሚቆም የሚገኝ የታመነ ባለሟል መሆኑን ያጠይቃል። ቅዱስ ያሬድ ገብር ያለውን ለሰው ሰጥቶ አንድም ሰው አምላክ ፣ አምላክ ሰው የመሆኑን ነገር የምሥራች የተናገረ እርሱ ከመሆኑ ጋር አያይዞ ገብርኤል ማለት ብእሲ ወአምላክ ሰውና አምላክ ማለት ነው ብሎ ተርጉሞታል “ገብርኤል ብሂል ብእሲ ወአምላክ እምኀበ እግዚአብሔር ዘተፈነወ ላእክ እንዲል። (ዚቅ ዘታኅ/ገብ) 

         ሊቃውንት በየድርሳናቸው በያባባላቸው ጠርተውታል አትናቴዎስ ቅዱስ ያሬድ መልአከ ሰላም ፣ ቅዱስ ኤፍሬም መልአክ ዜናዊ ፍሡሐ ገጽ፣ አባ ሕርያቆስ መልአክ ብርሃናዊ ብለውታል። (ሃይ/አበ፣ ድጓ፣ ወዳ.ማ ዘረ ፣ ቅዳ.ማ ቁ.፵፭) መልአከ ሰላም አሉት መላእክት በተፈጠሩበት በዕለተ እሑድ ጌታ አእምሮ ለብዎ አላቸውና ተመራምረው ሀልዎቴን ይወቁ ብሎ ብሎ ፈጥሮ በተሠወረባቸው ጊዜ መላእክት ማን ፈጠረን ሲባባሉ ሳጥናኤል በመዐርግ ከፍ ማለቱን አይቶ ከበላዩም ሌላ ማንም አለመኖሩን ተመልክቶ እኔ ፈጠርዃችሁ ቢላቸው ከርሱ ነገድ ሲሶው ነው ብለው ሲሰግዱለት ሲሶው ይሆን አይሆን ብለው ጥርጥር ውስጥ ሲወድቁ ሲሶው ፈጣሪ ይኑርም አይኑርም ሳይመረምሩ ቀርተዋል፤ የተጠራጠሩትን ሊያሳምን ፈጥሬ ላሳያችሁ ብሎ እጁን እሳት ውስጥ ጨመረው ፈጅቶት ጮኸ በዚህ ምክንያት በመላእክት ከተሞች ሽብር ጸና። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል እንደ ታማኝ አርበኛ ፈጣሪያችንን እስክናገኘው ድረስ በያለንበት እንጽና ብሎ አጽናንቷቸው ሽብር ተወግዶ ኋላም ጌታ ከወደ ምሥራቅ ተገልጸላቸው ሰላም ሰፍኗልና። (መቅድም) 

        መልአክ ዜናዊ ፍሡሐ ገጽ አለው ደስ ያለው በፊቱ ደስታ የተሳለበት ባለምሥራች መልአክ ሲል ነው “ወይሬእዩ ሠናይተ እንተ ትከውን ለካልዓን ከመ ዚአሆሙ ይእቲ እንዲል (ሃይ/አበ) መላእክት ለሰው በሚደረግ መልካም ነገር ሁሉ ደስ ይሰኛሉና እርሱም ካልዓይ ሊቀ መላእክት ቅሩበ አምላክ ነውና ልደተ ሶምሶንን ለማኑሄ ልደተ ዮሐንስን ለዘካርያስ ሊያበስር በተላከ ጊዜ ደስ በሚያሰኝ ግርማ ነውና ይልቁንም ለዓለሙ ሁሉ ደስታ የሚሆን የጌታን መወለድ ተፈሥሒ ተፈሥሒ ብሎ ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም በተወልደም ጊዜ ልደቱን “ወነዋ እዜንወክሙ ፍሥሓ ዘይከወን ለክሙ ወለኵሉ ዓለም እነሆ ለእናንተና ለዓለሙ ሁሉ ደስታ እነግራችኋለሁ ብሎ ለእረኞች  አብስሯልና። ሉቃ ፩፥ ፳፰ ፣ ፪፥፲

        መልአክ ብርሃናዊ አለው ተፈጥሮው ከብርሃን አካላዊ ነውና አንድም መላእክተ ጽልመት አሉና ከነዚያ ሲለየው አንድም የብርሃን ጌታ ባልሟል ነውና። መጻሕፍት ቅዱስ ሚካኤልን መጋቤ ብሉይ ሲሉ ቅዱስ ገብርኤልን መጋቤ ሐዲስ ብለውታል በብሉይ አልነበረም ወይም ለተልዕኮ አልወጣም አልወረደም ማለት ግን አይደለም ሁሉ በሁሉ ሳሉ የብሉዩን ለአብ የሐዲሱን ለወልድ ሰጥቶ አድሎ መናገር ልማድ እንደሆነ። ከመላእክት ተለይቶ የጌታን ሰው የመሆን ምሥጢር ለእመቤታችን እንዲያበስር መመረጡ ይህ ጸጋው ክብሩ ነውና የሐዲስ ኪዳን መጀመር በጌታ መጸነስ መወለድ ነውና ይህን ጸጋውን ለማዘከር መጋቤ ሐዲስ ብለውታል። በብሉይ ስለተፈጸመ ተልዕኮው ግን በብዙ ክፍላተ መጻሕፍት ተጽፏል። ለአብነትም ያህል ለዳንኤል የራእዩን ፍቺ ይነግር ዘንድ መላኩ ተጽፏል። ዳን ፰፥፲፮ ሎጥን ሰዶም ከጠፋችበት እሳተ መዐት ለማዳን ከተላኩት መላእክት (ዘፍ፲፱፥፩)አንዱ እርሱ መሆኑም በመተርጉማነ መጻሕፍት የተገለጸ ሲሆን ቅዱስ ያሬድም ከጌታ ዘንድ ተልኮ በዕፀ ጳጦስ ዘንድ ሙሴን ያነጋገረው መልአክ (ዘጸ፫፥፪ )ቅዱስ ገብርኤል መሆኑን መስክሯል። ወረደ መልአከ እግዚአብሔር ኀበ ማርያም ድንግል ዘተናገሮ ለሙሴ በኀበ ዕፀ ጳጦስ እንዲል ድጓ። 

       ሠለስቱ ደቂቅን በእሳት ከመቃጠል የመታደጉ ታሪክም ሌላው ማስረጃ ነው። ይህም በየዓመቱ ታኅሣስ ፲፱ ቀን የሚከበረው ዓመታዊ በዓል ከበዓለ ሢመትነቱ በተጨማሪ በዓሉ የሚከበርበት ዐቢይ ምክንያት በመሆኑ ታሪኩን በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን። ሠለስቱ ደቂቅ ንጉሠ ባቢሎን ናቡከደነጾር ከእስራኤል ማርኮ ወስዶ በከተማው ያኖራቸው ከነበሩ ደቂቀ እስራኤል ወገን ናቸው ስማቸው አናንያ አዛርያ እና ሚሳኤል ይባላሉ ንጉሡ ግን ጥበበ ባቢሎን ተምረው ጣዖታቱን እያገለገሉ እንዲኖሩ አጭቷቸው ስለነበረ ለቤል ለዳጎን የተሰጣችሁ ናችሁ ሲል ስማቸውን ለውጦ ሲድራቅ ሚሳቅ አብደናጎ ብሏቸዋል። ተማርከው በባዕድ ሀገር ቢኖሩም ሕገ ኦሪትን ጠብቀው ሥርዓተ አበውን አክብረው ይኖሩ ነበር ፤ ሰውነታቸውንም ከደስታ ለይተው ጥሬ እንብላ በማለት ጸንተው ነበር። 

      ዳንኤል የንጉሡን የተሠወረ ሕልም ከፈታ በኋላ እርሱን በቤተ መንግሥት እነዚህንም ሦስት ወጣቶች በሦስት አውራጃዎች ላይ ሾሟቸው። ባቢሎናውያን በዚህ ቀንተዋልና ሊያጣሏቸው ምክንያት ይሹ ጀመሩ። የኋላ ኋላ ማጣያቸው አምልኮ እግዚአብሔር መሆኑን አውቀው ንጉሡን ወዳጅ ጠላትህን እንድታውቅበት በራእይ እንዳየኸው ያለ ታላቅ ምስል አሠርተህ በአዱራን ሜዳ አቁም ከዚያም ለዚህ ምስል ያልሰገደ ቤቱ ይበርበር ብለህ አዋጅ አስነግር አሉት፡፡ እርሱም እንደመከሩት አደረገ ሕዝቡም የእንቢልታ የጡሩንባ ድምጽ በሰሙ ጊዜ እየወደቁ ለወርቁ ምስል ሰገዱ እኒህ ሦስት ወጣቶች ግን አንሰግድም ብለው ቀሩ። ባቢሎናውያኑ ንጉሥ ላቆመው ምስል አንሰግድም ብለዋል ብለው ለንጉሥ ከሰሷቸው።

      ናቡከደነጾር አስጠርቶ እውነት ነው ላቆምሁት የወርቅ ምስል አንሰግድም ብላችኋል? መኑ ያድኅነክሙ እም እዴየ ከእጄ ማን ያድናችኋል? ብሎ በሚያስፈራ ግርማ ጠየቃቸው። እነርሱም ሀሎነ አምላክነ ዘፈጠረ ኪያከ ወኪያነ አንተንም እኛንም የፈጠረ አምላካችን አለልን እርሱ ያድነናል አሉት። 

       ናቡከደነጾር በመንግሥት ይበልጣቸዋል ሀልዎተ እግዚአብሔርን በማወቅ ግን ከእነርሱ የተካከለ አልነበረም ፤ በሀብት ይበልጣቸዋል በዕውቀት በጥበብ ግን ከእነርሱ ያነሰ ነበረና የእግዚአብሔር መጠራት በእግዚአብሔርም መተማመናቸው አበሳጭቶት የዕቶኑን እሳት ጨምረው ጨማምረው እንዲያነዱት አዘዘ ፤ የእሳቱ ወላፈን ሽቅብ እየተወረወረ ፵፱ ክንድ የሚረዝሙ ዛፎችን ቅርንጫፍ ቅርንጫፋቸውን በላ። ወዲያው ወስዳችሁ ከዕቶኑ ጣሏቸው ብሎ ትእዛዝ ሰጠ። ኃያላን ተመርጠው እየገፈተሩ ወስደው ከተቷቸው፤ ወርዋሪዎቹ ከዕቶኑ ባይገቡም በውጭ ሆነው ተቃጠሉ እነ አናንያ ግን እነርሱ በተጣሉባት ቅጽበት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ፈጥኖ ወርዶ ነበልባሉን በበትረ መስቀል ቢባርከው ለሰውነት የሚስማማ እንጂ የማያቃጥል እሳት ሆኖላቸው በውስጡ ሆነው ያመሰግኑ ጀመሩ በአዲስ ድርሰት በአዲስ ምስጋና “ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ ስቡሕኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ ለዓለምየአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ከፍ ከፍ ያለም ነው“ እያሉ፤ ይትባረክ የሚለውን ፮ ቱን ይባርክዎ የሚለውን ፴፫ቱን ምስጋና ያመሰገኑት ያን ጊዜ ነው።

        በማግሥቱ ናቡከደነጾር ከሰገነቱ ሆኖ ሲመለከት በእሳት ውስጥ እየተመላለሱ ሲያመሰግኑ አየ ወዲያው ባለሟሎቹን ጠርቶ ትናንት ሦስት ሰዎች አሥረን ወደ ዕቶኑ ጥለን ነበር አሁን ግን አራት ሆነው አያቸዋለሁ አራተኛውም የአማልክት ልጅ ይመስላል ብሎ ጠየቀ። ወዲያውም ወደ ዕቶኑ ሄዶ እናንተ የእግዚአብሔር ባለሟሎች ሲድራቅ ሚሳቅ አብደናጎ ኑ ውጡ አላቸው ጸጉራቸው ሳያር ልብሳቸው ሳይቀነብር በፍጹም ደኅንነት ተጠብቀው ወጥተዋል። ንጉሡም በተፈጸመላቸው ተአምራት ወደ ሃይማኖት ተስቦ መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ የሲድራቅ የሚሳቅ እና የአብደናጎ አምላክ የተመሰገነ ይሁን ብሏል፤ ሕዝቡም በእግዚአብሔር ቅዱስ ስም ላይ የስድብና የነቀፌታ ንግግር እንዳይናገሩ አውጇል። ዳን፫፥ ፩-፴ 

          የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል አማላጅነትነት ጥበቃ አይለየን ፤ በባዕድ ሀገር ሳይበድሉ የተበደሉ ሳይገፉ የተገፉ በስደትና በምርኮም ሆነ መከራ የሚቀበሉ ወገኖቻችን ያጽናናልን፤ ከሀገራቸው ወጥተው በስደት ሳሉ የሰይፍ ራት የጥይት ሲሳይ የሆኑትን አውሬ የበላቸው ባሕር ያሰጠማቸውን ከፈጣሪው አማልዶ ዕረፍተ ነፍስ ፤ ያሰጥልን ሀገራችን ኢትዮጵያን ሕዝበ ክርስቲያኑና አንዲት ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን።    

ወስብሐት ለእግዚአብሔር